ኅዳር 2 ፣ 2015

የብርቅዬ ግንፍል - ለአራት አስርት ዓመታት ያልነጠፈ የአዳማ በረከት

City: Adamaየአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

ድምጻዊ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ) “የትዝታው ፈረስ” በተሰኘው ሙዚቃው ውስጥ እንዲህ ሲል አዚሟል፥ “የሳር ተራው ሲሳይ ያስመሸኝ ካራዳ፣ የድሃ እራት ንፍሮ የብርቅዬ ጓዳ”

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የብርቅዬ ግንፍል - ለአራት አስርት ዓመታት ያልነጠፈ የአዳማ በረከት
Camera Icon

ፎቶ፡ ከተስፋልደት ብዙወርቅ (ከቦሎቄ እና ከበቆሎ የሚዘጋጀው ንፍሮ)

“ወላሂ በሃቅ ነው የምሸጠው። አላህ ነው የሚያውቀው። ሲያከስረኝ ነው ዋጋ የጨመርኩት” ይላሉ ወ/ሮ ብርቄ በእናትነት የደግነት ስሜት። በአሁን ወቅት ከ5 ብር ጀምሮ የ10፣ የ15 ብር እያለ በሚቀጥል ዋጋ የብርቅዬ ንፍሮ ለብዙዎች ምሳና እራት ሆኖ ቀጥሏል።

ወ/ሮ ብርቄ ከብዙ የአዳማ ነዋሪዎች ጋር ያስተዋውቃቸውን፣ በፍቅርና በአክብሮት “ብርቅዬ የደሃ እናት” ያስባላቸውን የንፍሮ ስራ የጀመሩት በ1977 ዓ.ም ነው። ይህን ከ37 ዓመታት በላይ የዘለቀውን ታሪክ የአዳማው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር እንዲህ ያስቃኘናል።   

አዳማ ውስጥ በተለምዶ 06 በትክክለኛ መጠሪያው ደግሞ “ጀሚያ አል ሃቢብ መስጂድ” አካባቢ በብዙ ነገሮች ታዋቂ ነው። የጀሚያ አል-ሃቢብ መስጅድ ሚናራ ላይ የተሰቀለው የድምጽ ማጉያ የዝሁር ሰላት አዛን (የስግደት ጥሪ) አስተጋብቶ ከተሰገደ በኋላ የመስጂዱን አጥር ተደግፎ የተዘረጋው የበረከት እጅ ደግሞ ብዙዎችን ሊያጠግብ ይዘጋጃል። በጣም አነስተኛ በሚባል ዋጋ ምሳ፣ መክሰስና እራት ይሆናል፤ የብርቅዬ ግንፍል (የብርቅዬ ንፍሮ)።

ዛሬ ዛሬ “ግንፍል” የሚለው ቃል ብዙም አይዘወተርም ይልቅም “ንፍሮ” በሚል ተተክቷል። ብርቅዬ ማለትም ወ/ሮ ብርቄ አህመድ ያለፉት 37 ዓመታትን በአዳማ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግንፍል እያዘጋጁ በመሸጥ የሚታወቁ እናት ናቸው። 

ወ/ሮ ብርቄ እድሜያቸው ወደ ሰማንያ የተጠጋ፣ የልጅ ልጅ ያዩ አያት ናቸው። ቢሆንም ፍቅር እና ውዴታቸው የእናት ያህል የሆነበት የአዳማ ነዋሪ 'እማማ' ወይም 'እትዬ' ማለቱ ትቶ እንዲሁ እንደ ቤተሰብ በነጠላው 'ብርቅዬ' እያለ ይጠራቸዋል።

ብርቅዬ ማናት?

“አርቦዬ የተባለ ቦታ አርሲ ውስጥ ተወለድኩ” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ አህመድ እድሜዬ ከ80 ከፍ ቢል እነጂ እንደማያንስ ይናገራሉ። “በ3 ዓመቴ አባቴ ሲሞት ከእናቴ ጋር ወደ እዚሁ መጥቼ ሳር ሰፈር አደግኩ” ይላሉ።

“ያለ እድሜዬ በ7 ዓመቴ ነው ለጋሃር ቢስ ቤት መጋዘን ውስጥ ቦሎቄ ለቀማ ስራ የጀመርኩት። ከዛ በ18 ዓመቴ ተዳርኩ” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ በትዳር ህይወት 5 ልጆች ማፍራታቸውን ይናገራሉ።

“ብዙ ስራ ሰርቻለሁ። ሽሮ እና በርበሬ መነገድ፣ ፓስቲ መጥበስ፣ እንጀራ ጋግሮ ማስረከብ ሰርቻለሁ” ይላሉ። የንፍሮ ስራው ሃሳብ የመጣው በ1977 ዓ.ም እንደሆነ ወ/ሮ ብርቄ ያስታወሳሉ።

“ከሃጂ አብዱ መጋዘን ቦሎቄ ገዝቼ ጀመርኩ። በድስት ስል፣ በማሰሮ ስል አሁን በቀን አምስት ጎላ ድስት እጥዳለሁ” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ ስራውን የጀመሩት አሁን መብራት ኃይል በሚባለው አካባቢ፤ የድሮው ሀገር አቋራጭ መናኸሪያ እንደነበር ይናገራሉ። በዚያ ቦታ ሰፈሩ እስኪፈርስ ድረስም መስራታቸውን ይናገራሉ። 

በመቀጠል ወደ 08 ተዛውረው ሰርተው በመጨረሻም አሁን ወዳሉበት የጀምያ አል-ሃቢብ መስጂድ አካባቢ መምጣታቸውን ያስረዳሉ።

ንፍሮው በመዋናነት ቦሎቄ እና ቦቆሎ ተቀቅሎ የሚዘጋጀ ሲሆን ጨው እና ሚጥሚጣ እንደማጣፈጫ ይጨመርበታል። ንፍሮውን ለቀን ሽያጭ ለማድረስ ለሊት 9 ሰዓት ጀምሮ ይቀቀልና ረፋድ 5 ሰዓት ተጠንፍፎ ለሽያጭ ይዘጋጃል። ተመጋቢው እንደፍላጎቱ እዛውም ተቀምጦ ይመገባል አልያም ወደ ቤቱ ይወስዳል። 

በአሁን ወቅት ከ5 ብር ጀምሮ የ10፣ የ15 ብር እያለ በሚቀጥል ዋጋ የብርቅዬ ንፍሮ እየተሸጠ ይገኛል። “ወላሂ በሃቅ ነው ምሽጠው። አላህ ነው የሚያውቀው። ሲያከስረኝ ነው ዋጋ የጨመርኩት” ይላሉ ወ/ሮ ብርቄ በእናትነት የደግነት ስሜት። 

ታዋቂው ድምጻዊ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ) አዳማ ካፈራቻቸው ጥበበኖች አንዱ ነው። ድምጻዊው ስለልጅነቱ የአዳማ (የናዝሬት) ትዝታው ለአድማጭ ባደረሰው “የትዝታው ፈረስ” በሚለው ሙዚቃው ውስጥ “የድሃ ራት ንፍሮ የብርቅዬ ጓዳ” ሲል የብርቅዬን የደሃ እናትነት ከፍ አድርጎ አዚሟል።

“ወጣቱን አመሰግናለሁ። በሄድኩበት ሁሉ ይንከባከቡኛል። ደህንነቴን የሚጠይቁ፣ መንገድ ቢጠፋኝ የሚያሳዩ፣ መጥተው ሚጠይቁኝ ልጆች አሉኝ” ይላሉ ወ/ሮ ብርቄ በፈገግታ ተሞልተው።

ያለፉት 37 ዓመታት ንፍሮ በመሸጥ ብዙዎችን መመገብ የቻሉት ወ/ሮ ብርቄ፤ በዚሁ ስራ የበዛ የሰው ፍቅር እንዳተረፉበት ይናገራሉ። “አንዱ ከጅማ 'ዳኛ ነኝ' የሚል ሰው አንድ ቀን ቡና ይዞ ቤቴ መጣ” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ “ተማሪ ሆኜ አንቺ ጋር ነበር ብዙ ያሳለፍኩት ብሎ አመስግኖ ጠይቆኛል” ሲሉ ከብዙ ገጠመኛቸው አንዱን መዘው አጫውተውናል።

ወ/ሮ ብርቄ የውጪውን ስራ ካቆሙ አራት ዓመት ሆኗቸዋል። እርሳቸው ተክታ ልጃቸው እየሰራች ትገኛለች። “አይኔን ከሚያመኝ በቀር ለእርጅና አልተሸነፍኩም። ቤት ውስጥም እሰራለሁ” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ “ኩራት ብላሽ (ከንቱ) ነውና ወጣቶች ታትራችሁ ስሩ” ሲሉ ይመክራሉ።

በአሁን ወቅት ወ/ሮ ብርቄ ከጀሚያ አል-ሃቢብ መስጊድ ጀርባ በሰሩት መኖሪያ ቤታቸው ይኖራሉ። ከንፍሮ ስራው ጎን ለጎን የንፍሮ ተረፈ ምርት የሆነው ንፍሮ የተቀቀለበት ውሃ “ለከብቶች ተስማሚ ነው” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ የወተት ላሞች በማርባት የወተት ተዋጽዎችን ለአካባቢው ገበያ ያቀርባሉ።

የብርቅዬን (የወ/ሮ ብርቄን) የስራ ትጋትና ደግነት ከልጅ እስከ አዋቂው በአድናቆት ሲናገር ይደመጣል።

አቶ ጸጋዬ ማሞ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖጂ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኛ ነው። ተወልዶ ያደገው ትልቁ መስጊድ ተብሎ በሚታወቀው ጀምያ አል ሃቢብ መስጂድ አካባቢ ነው። የሃምሳ ዓመት ጎልማሳው ስለብርቅዬ ንፍሮ አውርቶ አይጠግብም። 

“የብርቅዬ ንፍሮ በ5 ሳንቲም በነበረ ሰዓት ነው መብላት የጀመርኩት” ይላል ጸጋዬ።  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን የከፋ የረሃብ ዘመን አስታውሶ “በወቅቱ ብርቅዬ ማለት እርዳታ ማስተባበሪያ ናት ማለት ይቻላል” ሲል ይገልጻል።  

አብዲ ጀማል እድሜው በአስራዎቹ ውስጥ የሆነ ታዳጊ ነው። ብርቅዬ ንፍሮ ከምትሸጥበት አካባቢ የሀይማኖት መጽሐፍት መሸጫ ሱቅ ውስጥ ይሰራል።

“ብርቅዬ አዳማን ደግፋ የያዘች ምሰሶ ናት” የሚለው አብዲ፤ ብዙ ሰዎች ሲመጡ እንደሚያይ አጫውቶናል። ከቀን ስራ ሰራተኛ ወዛደሮች እስከ ቅንጡ መኪና ባለቤቶች ድረስ መጥተው ሲገዙ እንደሚያይ ይናገራል።

ነጂብ ቡሽራ በምዕራብ ሀረርጌ የጭሮ ከተማ ነዋሪ ነው። “ሱስ ሆኖብኝ ከወዳጆቼም ጋ ብቻዬንም ወደ ብርቅዬ ጋ እመጣለሁ” ያለው ነጂብ ብርቅዬ ለብዙዎች ድጋፍ እንደሆነች ይናገራል። 

ምሳ ሰዓት ላይ የሚጀመረው የንፍሮ ሽያጭ አንዳንዴ እስከ ማታ 2 ሰዓት ድረስ እንደሚቆይና ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን የሚናገረው ነጂብ “ምርቃቱ ራሱ ያጠግባል” ይላል።

የጎልማሳው የአቶ ጸጋዬ እና የታዳጊው አብዲ አስተያየት ለዘመናት የዘለቀውን የብርቅዬ ንፍሮን ተወዳጀነትን የሚያሳይ ነው። ወ/ሮ ብርቄ ለደንበኞቻቸው የሚያሳዩት የእናትነት ፍቅርና ደግነት በብዙ የአዳማ ነዋሪዎች ዘንድ ዛሬም ድረስ በመልካም የሚታወስ ሆኖ እንደዘለቀ ብዙዎች ይመሰክራሉ።   

መዲናዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ የሀገራችን ከተሞች ውስጥ በመንገድ ዳር የሚሸጡ ንፍሮ፣ ድንች፣ ቆሎ፣ ሳንቡሳ፣ ቦቆሎና መስል ምግቦች ለሚሊዮኖች መሰረታዊ የዕለት ፍጆታ መሆናቸው ይታወቃል። አብዛኞቹ ይህን ስራ የሚሰሩት ሴቶች በመሆናቸው በእናትነት ስሜት ሁሉን እንዳቅሙ በመመገብ አለኝታ ሆነው ዘልቀዋል።

አስተያየት