ሚያዝያ 20 ፣ 2014

ያለ ምንም ቴክኖሎጂ ትክክለኛ ሰዓት የሚናገሩት የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮች

“ግርማ ሰዐቱ” በመባል የሚታወቁት አቶ ግርማ ተስፋዬ ሰዓት እና ደቂቃ ሳይሳሳቱ የሚናገሩ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ያለ ምንም ቴክኖሎጂ ትክክለኛ ሰዓት የሚናገሩት የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

አቶ ግርማ ተስፋዬ ይባላሉ። ትዉልዳቸዉ አዲስ አበባ ሲሆን በልጅነታቸዉ ነዉ ወደ ሐዋሳ ከተማ የመጡት። ምንም አይነት የእጅ ሰዓት ወይም ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ ሳይጠቀሙ ትክክለኛ ሰዓትን ይናገራሉ፤ በዚህም በአከባቢው ማህበረሰብ "ግርማ ሰዓቱ" በመባል ይታወቃሉ። 

የ48 ዓመት እድሜ ጎልማሳ የሆኑት አቶ ግርማ የሰዓት አቆጣጠርን በመለማመድ በቃላቸው መገመት የጀመሩት ገና በልጅነታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። “አስረኛ ዓመት እድሜዬ ላይ ስደርስ ሰዓት በትክክል መናገር ጀምሬ ነበር፤ ሰዓት እና ደቂቃ የምናገረዉ በግምት አይደለም እንዲሁ ማወቅ ስለምችል ነው” ይላሉ፤ በግምት ቢሆን ሊሳሳቱ እንደሚችሉ በመጠቆም።

በተለምዶ “ግርማ ሰዐቱ” በመባል የሚታወቁት አቶ ግርማ ተስፋዬ በሐዋሳ ከተማ ኮረም ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው።  በተለምዶ ሰዓት በትክክል ከመናገር በተጨማሪ የአየር ትንበያም በእርግጠኝነት ሲናገሩ የሚያዉቋቸዉ የአካባቢው ሰዎች ስለ እርሳቸዉ ይመሰክራሉ።

ወ/ሮ አበበች አዲሴ የአቶ ግርማ ጎረቤት ናቸዉ። ከሃያ ዓመት በላይ በጉርብትና ኖረዋል። “በተለምዶ ሰዓት ከመናገራቸዉ በተጨማሪ ዝናብ መዝነብ ወይም አለመዝነቡን በትክክል ሲተነብዩም አውቃለሁ” በማለት ስለ አቶ ግርማ ልዩ ክህሎት ነግረውናል።  

ከአቶ ግርማ ጋር በመንገድ ላይ ሲገናኙ “ሰዓት ስንት ሆነ?” ብሎ መጠየቅ ለአካባቢው ነዋሪ ከትንሽ እስከትልቅ የተለመደ ተግባር ነው። እሳቸዉ ሰዓቱን ሲናገሩ ትክክል መሆኑን  ለማረጋገጥ የእጅ ሰዓታቸው በማየት የሚያመሳክሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ምንግዜም እንደማይሳሳቱ ያረጋግጣሉ። 

አቶ ሽመልስ በቀለ የአከባቢው ነዋሪ ሲሆኑ ከአቶ ግርማ ጋር ከተዋወቁ ከአስር ዓመት በላይ እንደሆናቸዉ አጫውተውናል። “አቶ ግርማ ከድሮ ጀምሮ ሰዓት በእጃቸዉ ሳይኖር በተለምዶ ትክክለኛ ሰዓት የሚናገሩ ሰዉ ናቸዉ፤ 'በጭንቅላቴ ዉስጥ ሰዓቱ ሲንቀሳቀስ ያቃጭላል'  የሚሉት ንግግር ሁሌም አልረሳውም” በማለት ያስታዉሳሉ። 

በቀለም ትምህርታቸዉ ከሰባተኛ ክፍል በላይ መዝለቅ ያልቻሉት እና በተለምዶ ሰዓት የሚናገሩት አቶ ግርማ ተስፋዬ አሁን ላይ የሚኖሩት ከአያታቸዉ ጋር ነዉ። ትዳር እንዲሁም ልጆች እንደሌላቸውም ገልጸዋል። 

“እኔ ትክክለኛ ሰዓት በመናገሬ አንዳንዶች ከጥንቆላ ጋር አያይዘዉ ሲናገሩ እሰማለሁ” የሚሉት አቶ ግርማ እዉነታዉ ግን ከፈጣሪ የተሰጣቸው ጸጋ መሆኑን ይናገራሉ። ለተቀረዉ የሀገሪቱ ክፍል በርካቶች የተደነቁበትን የእርቸዉን ጥበብ ማሳየት እንደሚፈልጉ ነገር ግን እድሉን ማግኘት እንዳልቻሉም አስረድተውናል። 

አስተያየት